Tuesday, July 16, 2013

ትናንት አዲስ አበባ፡ዛሬ ደሴ እና ጎንደር ማነህ/ሽ ባለሳምንት?

እድሜ ለአንድነት፡አስተነፈሰን

ነበር ያሉት ባለፈው እሁድ ሃምሌ 8 2005 የዴሴን ጎዳናዎች ያጥለቀለቁት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ያለው የህውሃት መንግስት የሚያደርገውን አፈናና ወከባ እንዲያቆም ለመጠየቅ ሰላማዊ የወጡ የአንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ ደጋፊዎች እና አባላት። እኔ ደግሞ እድሜ ለሰማያዊ ፓርቲ ብያለሁ፡ ምክንያቱም ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን ከ 97ቱ ምርጫ በኋላ በገዥው ፓርቲ ታግቶ የቆየውን ህገመንግስታዊ መብት ባይሰብር ኖሮ ባለፈው እሁድ በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ያየናቸውን ደማቅ እና
እጅግ ፍጹም ጨዋነት የተሞላባቸው ሰላማዊ ሰልፎችን ለማየት ያለው እድል በጣም ውሱን ነበር። በሁለቱም ከተሞች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ያላንዳች ችግር እና በተያዘላቸው መርሃግብር መሰረት በሰላም የተጠናቀቁ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና ፖሊስ መንገዶችን በመኪና በመዝጋት የየከተማዎቹ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፉን እንዳይቀላቀሉ ያደረጉት ጥረት ቢከሽፍም በእለቱ በጎንደር ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ይዘንብ የነበረው ዝናብ ሰላማዊ ሰልፉ መጠናቀቅ ከነበረበት ሰዓት ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅ ማድረጉን በስፍራው የነበረው የአንድነት ፓርት ልሳን ማለትም የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ዘጋቢ አስታውቋል።

መንግስት ለምን እነዚህ ሰላማዊ ሰልፎችን ፈቀደ?

ይህ በጣም የሚያከራክር ጥያቄ ባይሆንም፡ አንዳንድ የዋሃን የሚሉት ግን አዲሱ "ጠቅላይ ምኒስትራችን" ከቀሞው የተለየ ታጋሽነትና አስተዋይነት ስላላቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ከነእነዚህ አንዱ በቅርቡ እዚህ አገር ያገኘሁዋቸው አንድ በኢትዮጵያ የስራ ጊዚያቸውን የጨረሱ ምዕራባዊ ዲፕሎማት ይገኙበታል። እንደእኝህ ዲፕሎማት፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆኑ በስራ አጋጣሚ አግኝተዋቸው በማነጋገር ለማረጋገጥ ችለዋል ህምም አቶ መለስም እኮ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ አልነበሩም እንዴ? ወዲህም አለ ወዲያ አቶ ሃይለማርያም ስም እንጂ ይህ ነው የሚባል ስልጣን የሌላቸው ሲሆን ቀደም ሲል በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራውንም ሆነ ባለፈው እሁድ በአንድነት ፓርቲ የተዘጋጁትን ሰላማዊ ትግሎች የፈቀዱት እሳቸው ጥሩ ሰው በመሆናቸው ሳይሆን፡ ለፖለቲካ ፍጆታ እና በምዕራቡ ዓለም እና እርዳታ ለጋሽ አገሮች እየደረሰባቸው ያለውን ግፊት ለማስታገስ የታሰበ እንጂ ሌላ ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ልክ የእሁድ እለቱ ሰላማዊ ሰልፎች እንደተጠናቀቁ የእዚህ አገር ተወላጅ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትኩሳት በቅርበት የሚከታተል ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ መንግስት ስለሰላማዊ ሰልፎቹ የነበረው ምላሽ ምን ይመስል እንደነበረ ጠየቀኝ፡ እኔም ትንሽ ታገስ አልኩት፡ ጸሃዩ መንግስቴም አላሳፈረኝ በትናንትናው እለት እና ዛሬ የአንድነት ፓርቲ አባላት በጸጥታ ሃይሎች ታሰሩብኝ ያላቸው 42 ዓባላት (ሁለት ሴቶችን ጨምሮ) እማኝ ናቸው። ከታሰሩት መካከል ባለፈው የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ የነበረው ወጣት ይገኝበታል። ታዲያ ከዚህ ወዲያ የአቶ መለስን ራዕይ ማስቀጠል አለ? 

እኛስ ምን ያህል ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን?

የአዲስ አበባ፡የደሴ እና የጎንደር ከተሞች ነዋሪዎች በነቂስ በመውጣት በገዥው ፓርቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት ታግተው የቆዩ ህገመንግስታዊ እና በተፈጥሮ የተለገሱ መብቶቾቻቸው እንዲከበሩ፡ በህገወጥ መንገድ የታሰሩ ጋዜጠኞች፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፡አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች እንዲፈቱ፡ የህግ የበላይነት እንዲከበር፡በሙስና እና ስልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ሹመኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥያቄ አቅርበዋል (ሰሚ ጆሮ ካለ)። ዋናው ጥያቄ ግን እነዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ወደሌሎች ትላልቅ እና ትናንሽ ከተሞች እንዲሁም የገጠር ቀበሌዎች በመዳረስ ህብረተሰቡ እነዚህን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች በማንገብ ገዥው ፓርቲን እና ካድሬዎችን ለማፋጠጥ ምን ያህል ተደራጅቷል ነው። እነዚህ ወገኖቻችን ይህንን ፍርሃት በመስበር በሰላማዊ ትግል በመሳተፍ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ቆራጥነቱን አሳይቷል። እኛስ ምን ያህል ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን? መቼም ከህውሃትና እና ጭፍን ካድሬዎቹና ደጋፊዎቹ አበባ እና ዘንባባ ለተመሳሳይ የሰላማዊ ትግል ጥያቄዎች መጠበቅ ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ቀቢጸተስፋ ምኞት ነው። እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ በስልጣን ላይ እንደማይቆዩ ከ 97ቱ ታሪካዊ ምርጫ ስለተረዱ፡ የጠመንጃ አፈሙዝን በመጠቀም ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ወደኋላ እንደማይሉ ባለፉት 22 ዓመታት በገሃድ አሳይተዋል። ለስራ በመምህርነት ጋምቤላ ሄጄ የተዋቀቅሁት ዮሴፍ የሚባል በጣም ተረበኛና አሁን በህይወት የሌለ መምህር ነው የነገረኝ፡ ልጅቷ በጣም ቅምጥል ስትሆን ከቤት እስከ መኪና እንዲሁም ገንዘብ ሊገዛው የሚችል ቁሳዊ ነገር የተሟላላት ናት። ይህ ሁሉ ነገር ስላላረካት ጓደኛዋን አንድ ቀን እንዲህ ብላ ጠየቀችው 
ተፈቃሪ፡ ፍቅሬ አሁንስ ሁሉ ነገር ሰለችኝ (እግሯን የመስታወት ጠረቤዛው ዘርግታ፡በካውያ የለሰለሰ ጸጉሯን እያፍተለተለች) 
አፍቃሪ፡ እና ምን ይሻላል ውዴ?
ተፈቃሪ፡ በቃ አብዮት ግዛልኝ (ሙልቅቅ ባለ አማርኛ ቃላቱን እየጎተተች)
አፍቃሪ፡ እንዴ እሱን ደሞ ምን ልታደርጊው ሆዴ? (ግራ በመጋባት)
ተፈቃሪ፡ ላፈነዳው።(ኮስተር ብላ)
በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና፡አፈና፡እስራት፡እንግልት፡መከራ፡ስደት፡ስራ አጥነት፡ድህነት፡ከመሬት መፈናቀልና የፍትህ እጦት እግር ከወርች ጠፍረውት ዛሬ ጫንቋው እንዚህን ሁሉ መሸከም የማይችልበት ወቅት እና ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ከሰፋፊ መንገዶች፡ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች፡ምንም ጠብ ያለለት ነገር የለም፡ እንደዛች ሞልቃቃ ልጅ ግን አብዮት የሚገዛለት ሰው አይፈልግም... ህምም መስከረም ሳይጠባ...       



No comments:

Post a Comment