Wednesday, July 9, 2014

የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ የነበሩት እና በየመን መንግስት ባለስልጣናት ተላልፈው የተሰጡት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢቴቪ ላይ ቀረቡ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ለማምራት ባለፈው ሳምንት ሰንዓ ዓየር ማረፊያ ላይ አውሮፕላን ለመቀየር ሲሉ በየመናውያን የጽጥታ ሃይሎች ከተያዙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ እይታ የቀረቡት መንግስት በሚቆጣጠረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ዜና አቅራቢው ተመስገን በየነ ከወትሮው ለየት ባለ ንቃት እና ፈገግታ በመታጀብ አያቱ ሊሆኑ የሚችሉትን ግለሰብ አንተ እያለ በመዘርጠጥ ዜናው ሲያስደምጥ ነበር። አቶ አንዳርጋቸው በዚሁ ተቀናብሮ (ደበበ እሸቱ፡ ብርቱካን ሚዴቅሳ፡ ስዊድናውያን ጋዜጠኞቹን እና ሌሎችም በመቶ የሚቆጠሩ የቀድሞ እስረኞች ልብ ይሏል) በተሰጣቸው የንስሃ በሚመስል ቃለ ምልልስ ላይ፡ በእስር ላይ መዋላቸውን በጸጋነት እንደሚቀበሉት ሲናገሩ ተደምጠዋል። አጃኢብ ነው፡ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ስማ፣ ላልሰማ አሰማ ኢትዮጵያ ውስጥ ማእከላዊ የሚባል እስርቤት ሰላምህን የሚሰጥ ስለሆነ፡ ቦታ እንዳያመልጥህ ተሽቀዳደም። እቺ የተቀነባበረች ዜና የቀረበችው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአቶ አንዳርጋቸው ደህንነት እንዳሳሰባቸው በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ዓለምዓቀፍ ዘመቻ በጀመሩበት ሰዓት መሆኑ እነሱም ድራማ መስራት አይሰለቻቸው እኛም መመልከት ያሰኛል። የብሄራዊ ደህንነት ድርጅቱ በተጨማሪ ለተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች እና ደጋፊዎች፡ ለጋዜጠኞች እና ጦማሪያን እንዲሁም በዞን ዘጠኝ ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሙሉ በጸረሽብሩ "ህጋችን" ለእስር ከመዳረግ እንደማንድን በገደምዳሜ ተነግሮናል። ለማንኛውም ተመስገንን እንዲህ ያስፈነደቀው ዜና ከዚህ በታች በሚገኘው ቪድዮ ላይ መመልከት ይችላሉ። 

No comments:

Post a Comment