Monday, July 14, 2014

ከ ስድስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ጠበቃ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

Defendants’ lawyer Ato Amaha briefing the  crowd ‹‹ከቅዳሜ አራት ሰዓት ጀምሮ ደምበኞቼ በህገ ወጥ መንገድ መታሰራቸው መታወቅ አለበት ››
‹‹የአካል ነጻነታቸው እንዲከበርም ክስ እንመሰርታለን››
የአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር ለፖሊስ የሰጠው የ28 ቀን ቀጠሮ ቅዳሜ የሚያበቃበት በመሆኑ የዞን ዘጠኞችና የጋዜጠኞቹን ጉዳይ ሲከታተሉ የቆዩ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ጋዜጠኞች ቀደም ብለው ፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ደርሰዋል፡፡ምን ይወሰን ይሆን? በሁሉም ልብ የሚመላለስ ጥያቄም ነበር፡፡ከዘጠኙ ታሳሪዎች መካከል ስምንቱን በፍርድ ቤት ሲወክሉ የቆዩት ጠበቃ አምሀም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ቀደም ብለው ቅጥር ግቢው ተገኝተዋል፡፡
አራት ሰዓት እንደሚጀመር የተገመተው ችሉቱ እስከ አምስት ከሩብ ድረስ በሌሎች ጉዳዩች ተወጥሮ ቆይቷል፡፡ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ነፍጥ ባነገቱ ወታደሮች ታጅበው መምጣት የነበረባቸው ኪቦርድ አንጋቾች እስራት ያልበገረውን ተስፋቸውን እየዘሩ ሊመጡ አልቻሉም፡፡ሁኔታው አግራሞት የፈጠረባቸው የተወሰኑ ጋዜጠኞች ወደ መዝገብ ቤት በማምራት መረጃ ጠየቁ፡፡የተሰማው በግቢው ውስጥ የነበሩትን ጠበቃ አምሀ መኮንንን ጨምሮ ያስገረመ፣ ያሳዘነና ያሳፈረ ነበር፡፡ከጠበቃው ጋር ዳዊት ሰለሞን ያደረገው አጠር ያለ ቃለ ምልልስ እንደወረደ እነሆ፡፡
ጥያቄ---ወደ ፍርድ ቤቱ ሲመጡ በአእምሮዎ ያመላልሱት የነበረው ነገር ምንድን ነው?
ጠበቃ አምሀ---ምናልባት ምርመራ ባለመጨረሳችን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን ይላሉ እያልኩ ነበር፡፡ይህንን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ በምን አይነት መንገድ እንደሚመልስ ለማወቅም ፈልጌ ነበር፡፡የሆነው ግን በፍጹም ያልጠበቅነው ነገር ነው፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ያመሩ ጋዜጠኞች ‹‹የልጆቹ መርማሪ ነኝ ያለ ሰው ምርመራዬን በመጨረሴ ለአቃቤ ህግ አስተላልፊያለሁ›› በማለቱ መዝገቡ እንደተዘጋ እንደተነገራቸው እንደነገሩኝ እውነት መሆኑን አጣርቻለሁ፡፡
ጥያቄ --- ሁኔታውን እንደሰሙ ምን አደረጉ?
ጠበቃ አምሀ -- እኛ ከቀጠሮው ሰዓት ቀደም ብለን ግቢው ውስጥ ተገኝተን መርማሪው እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያቀርብ መስማት ነበረብን፡፡ በፍጹም እንዲህ አይነት መደረግ እንደሌለበት ቅሬታ እንደተሰማንና የተፈጸመው ነገር ህገ ወጥ መሆኑን ለዳኛው ተናግረናል፡፡
ጥያቄ -- ህገ ወጥ የሆነው ምንድን ነው?
ጠበቃ አምሀ --ለፖሊስ ልጆቹን ለተጨማሪ 28 ቀናት እንዲያስር ፈቅዶለት የነበረው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡እስካሁን ድረስ ደምበኞቼ የታሰሩት በፍርድ ቤት እውቅና ነው፡፡ከዛሬ አራት ሰዓት ጀምሮ ግን ደምበኞቼ የታሰሩት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመሆኑ እስራታቸው ህገ ወጥ ነው፡፡ፖሊስ ልጆቹን ፍርድ ቤት አቅርቦ ምርመራውን መጨረሱን ማስረዳትና ክስ የሚመሰርት ከሆነም ማሳወቅ ይገባው ነበር፡፡የሚመሰርተው ክስ ዋስትና የሚያስከለክልና የማያስከለክል መሆኑን መወሰን የነበረበት ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ይህ ሳይደረግ መዝገቡ ተዘግቷል መባሉ ህገ ወጥ ነው፡፡
ጥያቄ -- ከአሁን በኋላ ለደምበኞችዎ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ምንድን ነው?
ጠበቃ አምሀ -- ሰኞ ወይም ማክሰኞ የደምበኞቼ የአካል ነጻነት እንዲከበር ክስ እመሰርታለሁ፡፡ሰኞን የምንጠብቀው እንደተናገሩት ክስ የሚመሰርቱ ከሆነና የት እንደሚመሰርቱ ለማጣራት ነው፡፡
ጥያቄ --በ‹‹ሃብየስ ኮርፐስ›› ደምበኞችዎ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ክስ የምትመሰርቱት በየትኛው ፍርድ ቤት ነው?
ጠበቃ አምሀ --ክሱን የምንመሰርተው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ነው፡፡
ጥያቄ --ደምበኞችዎን በማዕከላዊ በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲጎበኙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ነገር ግን እስካሁን ድረስ አቤል ዋበላን ሰዎች ማግኘት እንዳልቻሉ እየተናገሩ ነው ምክንያቱን ለማጣራት ሙከራ አድርጋችኋል?

ጠበቃ አምሀ --- ከዚህ በፊት ልጆቹን በሳምንት አንድ ቀን እንዳናግራቸው ይፈቀድልኝ ነበር፡፡በዚሁ ቀን ስምንቱንም ልጆች የማናገር ዕድል ነበረኝ፡፡ አሁን ግን በአንድ ቀን ማናገር የምትችለው አንዱን ደምበኛህን ብቻ ነው ብለውኛል፡፡እንግዲህ ስምንቱን ደምበኞቼን ለማግኘት አራት ሳምንት ያስፈልገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጹም ህገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡ደምበኞቼ ከጠበቃቸው ጋር የመገናኘት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡
አቤልን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ ከመርማሪዎቹ ጋር ያልተስማማበት ነገር እንዳለ ሰምቼያለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን ከእርሱ አንደበት ለመስማት እርሱን መጀመሪያ ማግኘት ይኖርብኛል፡፡
ጥያቄ --ደምበኞችዎ በምርመራ ወቅት የማያምኑትን ወይም ያልተሳተፉበትን ጉዳይ እንደተሳተፉበት አድርገው ቃላቸውን በሃይል እንዲሰጡ ስለመደረጋቸው ይነገራል፡፡በሀይል የሰጡት ቃል በፍርድ ቤት የሚኖረው ተቀባይነት ምን ያህል ነው? በተለይ በጸረ ሽብር አዋጁ?
ጠበቃ አምሀ -- ለፖሊስ የሚሰጥን ቃል በተመለከተ የወንጀልና የሥነ-ስርዓት ህጉ በዝርዝር ይናገራሉ፡፡ለፖሊስ በሀይል እንደተሰጠ የተነገረበት የተጠርጣሪ ቃል ያን ያህል ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሰዎችም በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ ሊገደዱ አይገባም፡፡
ጥያቄ -- ቀሪዎቹ ደምበኞችዎ የፊታችን ሰኞ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተይዞባቸው ነበር፡፡ ከዛሬው በመነሳት ሰኞ የሚቀርቡ ይመስልዎታል?
ጠበቃ አምሀ ---- አይመስለኝም፡፡ እኛ ግን ቀጠሯችንን አክብረን በቦታው እንገኛለን፡፡ 
ምንጭ፡ Zone9

No comments:

Post a Comment